ፖለቲካዊ ሙስና እና የምርመራ ጋዜጠኝነት

በዓለምዓቀፍ ደረጃ ያለውን የፀረ-ሙስና እንቅስቃሴ በመምራት ላይ የሚገኘው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የሙስና ዓይነቶችን ጥቃቅን ሙስና፣ ግዙፍ ሙስና እና ፖለቲካዊ ሙስና በሚል በሶስት ይከፍላቸዋል፡፡

እንደ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ትርጉም አሰጣጥ ጥቃቅን ሙስና ማለት በህግ የተሰጠን ሃላፊነት በማንኛውም መንገድ ያለአግባብ መጠቀም ሲሆን መሰረታዊ ግልጋሎቶችን ለማግኘት ዜጎች ከተለያዩ በዝቅተኛ እና በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ሊፈጠር የሚችል አድሎአዊ አሰራርን ያጠቃልላል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ በሚገኙ የመንግስት አካላት የመንግስት ሃብትን ለመመዝበር በሚያመች መልኩ ፖሊሲዎችን እና ህጎችን ያለአግባብ ለመተርጎም ሲሞክሩ እና የመንግስትን መሰረታዊ አቋም እንዲፋለስ ሲያደርጉ ግዙፍ ሙስና እንደሚሆን ድርጅቱ ያስረዳል፡፡

ማንኛውም አይነት የፖለቲካ ዓላማን ለማራመድ በሚል በገንዘብ ወይንም በአይነት የሚፈጸም ሙስና ፖለቲካዊ ሙስና ሲሆን ፖለቲካዊ ሙስና የሚፈፀመው ደግሞ በአንድ ሀገር የፖለቲካ አናት ላይ በሚገኙና በሀገር ሀብት ስርጭት ወይም ታላላቅ ፖሊሲዎችና ህጎች ላይ ለመወሰን ሥልጣንና ኃላፊነት ባላቸው አካላት ነው፡፡

በዚህ የስልጣን ደረጃ የሚገኙ ግለሰቦች ወይንም አካላት ፖለቲካዊ ሙስና የሚፈጽሙት አንድም ሀብት ለማካበት ሲሆን አንድም ደግሞ የስልጣን ቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም ሊሆን ይችላል ፡፡

ይህ ማለት በአንድ በኩል ስልጣንን ተጠቅመው ያለአግባብ ሃብት ሲያከማቹ በሌላ መንገድ ደግሞ የህዝብንና የመንግስትን ገንዘብ በመጠቀም የተደላደለ የስልጣን ደረጃ ላይ ተቀምጦ ለመቆየት ያስችላቸዋል፡፡

ሆኖም ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናልም ሆነ ሌሎች በጉዳዩ ዙሪያ የሚሰሩ አካላት በሙስና ዙሪያ የሚወጡ በርካታ ጽሁፎች የሚያተኩሩት ስልጣንን ተጠቅሞ ያለአግባብ ሃብት ማከማቸት ላይ ሲሆን “ፖለቲካዊ ሙስና ስልጣንን ለማራዘም” የሚለው ጉዳይ ግን በደንብ ያልታየና ጠለቅ ያለ ጥናት የሚያስፈልገው ጉዳይ እንደሆነ ይስማማሉ፡፡

ፅሁፎች ሲባል በጥናት መልክ የተዘጋጁ፣ ለውይይት መነሻ የሚቀርቡ አሊያም በመገናኛ ብዙሃን የሚዘገቡትን የሚያካትት ሲሆን የዚህ ችግር በሃገራችንም ይስተዋላል፡፡

በኢትዮጵያ የፀረ-ሙስና እንቅስቃሴ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ የሚገኘው ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተለያዩ የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ጋር አድርጎት በነበረው ውይይት ፅሁፍ አቅራቢ የነበሩት እንግዳ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን በሙስና ዙሪያ የሚሰሩት ዘገባ በአብዛኛው ሃላፊነትን ያለአግባብ በመጠቀም ሃብት ምዝበራ ላይ ያተኮረ ሲሆን ያለአግባብ ስልጣንን ለማራዘም የሚደረግ እንቅስቃሴ ግን ትኩረት የተሰጠው እንዳልሆነ ተችተዋል፡፡

በዚህ አስተያየት መሰረት ሁለት መላምቶችን ማስቀመጥ የሚቻል ሲሆን የመጀመሪያው ስልጣንን ያለአግባብ ለማራዘም መሞከር በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ እንደ ፖሊካዊ ሙስና አለመታየቱ ነው፡፡

ሁለተኛው መላምት ደግሞ ፖለቲካዊ ሙስና መልካም አስተዳደር በማስፈን ሂደትም ሆነ በልማት ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ መገናኛ ብዙሃን ባለመረዳታቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡

የህዝብ ሃብትን በመመዝበር የስልጣን እድሜን ለማስረዘም የሚደረገው ጥረት ብዙውን ጊዜ አድሎን ወይንም ጥቅምን ያማከለ የፖለቲካ ስርዓት ይፈጥራል፡፡

ይህ የፖለቲካ ሙስና የፖለቲካ አመለካከትን ያማከለ የገንዘብ፣ የእቃ፣ የጥቅማ ጥቅም፣ የእድሎችና ገፈቶች ክፍፍልን ያካትታል ፡፡

ፖለቲካዊ ሙስና ባጠቃላይ በዋናነት ሊያስከትላቸው የሚችለው ጉዳቶች የተቋማት ወድቀት፣ ስልጣን በዘፈቀደ መንገድ መያዝ፣ የአምባገነንነት ባህሪን መላበስና የዜጎች ነጻነት መገደብ ናቸው ፡፡

ፖለቲካዊ ሙስናን ቴክኒካዊ ወይንም ቢሮክራሲያዊ በሆነ መንገድ ብቻ ማስቆም አሊያም መቀነስ እንደማይቻል ድረ-ገፅን መሰረት ያደረገው እና በጸረ-ሙስና እንቅስቃሴ ዙሪያ ለሚሰሩ ተቋማት እንደ መረጃ ማዕከል ሆኖ የሚያገለግለው u4 የተባለ ተቋም ይገልጻል፡፡

እንደ u4 መረጃ ፖለቲካዊ ሙስና ራሱን እንደቻለ አንድ የገበያ ችግር ወይንም የተበላሸ የአስተዳደር ሥርዓት ተደርጎ ሊታይም አይችልም ፡፡

የፖለቲካዊ ሙስናን ለመዋጋት ባለድርሻዎች የራሳቸውን ውስን ሚና የሚጫወቱበትን መንገድ ማፈላለግ የሚያስችል የፖለቲካ ባህሪ ያለው መፍትሄ ያሻል ፡፡

የችግሩን ምንጭ ማድረቅ ማለትም ፖለቲከኞች በፖለቲካ ስርዓቱ አግባብ ባልሆነ መንገድ የግል ጥቅማቸውን ሊያስከብሩ የሚችሉበትን መንገድ ማጥበብ ብሎም ለፖለቲካ ሙስና ሊኖር የሚችለውን ፍላጎት መቀነስ አንዱ አማራጭ ሊሆን ይችላል ፡፡

እዚህ ላይ ከባድ ፈተና ሊሆን የሚችለው ለህገወጥ ምዝበራ ክፍት የሆኑ ቀዳዳዎችን እንዴት መድፈን ይቻላል የሚለውና እንዴት ግልጽነትን፣ ተጠያቂነትንና የውስጥ ቁጥጥር ስርዓትን መፍጠር ይቻላል የሚሉት ናቸው፡፡

በዋናነት የህዝብን ጥቅም ማስከበር ስለሆነ ዓላማቸው መገናኛ ብዙሃን በተለይ በዚህ ረገድ ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን ለማስፈን የራሳቸውን የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚያስችል ሰፊ እና እምቅ ሃይል እንዳላቸው እሙን ነው፡፡

ነገርግን ይህም እንዳይሆን ፖለቲካዊ ሙሰኞች የመገናኛ ብዙሃን ነጻነትን በመገደብ የራሳቸውን ደህንነት እና የስልጣን መደላደል ሊያመቻቹ የሚችሉ ሲሆን ካላቸው የመወሰን አቅም ከፍተኛነት አንጻር መገናኛ ብዙሃኑንም ሆነ ጋዜጠኞችን ሊገዳደሩ ይችላሉ፡፡

የምርመራ ጋዜጠኝነት እጅግ አስፈላጊ ሆኖ የሚታየው እዚህ ላይ ነው፡፡

የምርመራ ጋዜጠኝነት ከተለመደው የጋዜጠኝነት ሙያ የሚለየው እጅግ ስልታዊ በሆነ አካሄድ በሚዘገበው ጉዳይ ላይ ጥልቅ ምልከታ፣ ዳሰሳ እና ትንተና ስለሚጠይቅ ሲሆን ሙስናን ለመዋጋት ጉልህ አስተዋጽኦ ሊጫወት ይችላል፡፡

እንዲህ አይነቱ የጋዜጠኝነት ሙያ ብዙውን ጊዜ የሚያተኩረው በከፍተኛ ደረጃ የተሰሩ ሙስናዎችን እንዲሁም ትላልቅ ድርጅቶች የሰሯቸውን ከፍተኛ ጥፋቶች በጥልቀት መርምሮ ይፋ ማውጣት ላይ ነው፡፡

በዚህም ምክንያት በጣም የተወሳሰቡ እና የተደበቁ ሙስናዎችን የሚያጋልጥ ሲሆን በመጨረሻም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ ሊያደርግ ይችላል፡፡

ሆኖም የምርመራ ጋዜጠኝነት እና በዘርፉ የሚሰሩ ጋዜጠኞች በርካታ ችግሮች ያሉባቸው ሲሆን ችግሮቹ ህልውናቸውን እስከመፈታተን እና የስራቸውን ጥራት እስከማበላሸት የሚያደርሱ ናቸው፡፡

በምርመራ ጋዜጠኝነት ዙሪያ ያለው ዋነኛ አጠያያቂ ጉዳይ ስራውን ለሚያከናውኑ ጋዜጠኞች እና ጥቆማ አቅራቢዎች በቂ ከለላ ሊሰጥ የሚችል ህግ አለመኖር ወይንም ያለው ህግ እና ተፈጻሚነት ደካማ መሆን ነው፡፡

ከዚህ ባለፈ የአቅም ውሱንነት፣ የፋይናንስ እጥረት እና መገናኛ ብዙሃኑ ውስጥ ሙስና መበራከት በሀገራችን እንዲያውም የለም የተባለውን የምርመራ ጋዜጠኝነት የበለጠ ድራሹ እንዲጠፋ እያደረገው ነው፡፡

በዚህም ምክንያት ፖለቲካዊ ሙስና መድሃኒት ያልተገኘለት ከባድ የሃገራችን ችግር ሆኖ እንዲቆይ ግድ የሚል ሲሆን የፖለቲካዊ ሙስና መጠንከር የምርመራ ጋዜጠኝነትን እንደሚያዳክመው ሁሉ የምርመራ ጋዜጠኝነት መጠንከር ደግሞ ፖለቲካዊ ሙስናን እንደሚያዳክመው ግን እሙን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኝነት መሰረቱን የጣሰ ተግባራዊው እውነታ

በመሰረቱ ስፖርት ሲባል ባህላዊውንም ዘመናዊውንም ጨምሮ አብዛኛዎቻችን ልንዘረዝራቸው የምንችላቸው የአካል እንቅስቃሴ እና ጥልቅ እሳቤን የሚጠይቁ ሁሉንም አይነት ጨዋታዎች ያጠቃልላል፡፡

ከመገናኛ ብዙሃን ፍላጎት አንጻር ስፖርት ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ የቆየ የመዝናኛ ፕሮግራም ሲሆን አሁን አሁን ደግሞ ከመዝናኛነትም ያለፈ ጉዳይን እየሆነ ይገኛል፡፡

ስፖርት እንደ አንድ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ምጣኔ-ሃብታዊ ጉዳይ ራሱን የቻለ ሰፊ ርዕሰ ጉዳይ እየሆነ የመጣ ሲሆን ሊሰጠው የሚገባው ግምትም ያን ያህል እየከበደ መጥቷል፡፡

በመሆኑም እነዚህን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ምጣኔ-ሃብታዊ ጉዳዮች ብቻ የሚተነትኑ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንዳሉ ሁሉ ስፖርታዊ ጉዳዮችን ብቻ የሚተነትኑ ጋዜጦች፣ ሬድዮኖች፣ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ ድረ-ገጾች እና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን በርካታ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያም ስፖርታዊ ጉዳይን ብቻ የሚተነትኑ ጋዜጦች እና ድረ-ገጾች ያሉ ሲሆን በሬድዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎችም ለስፖርታዊ ጉዳዮች ከሌሎቹ ርዕሰ-ጉዳዮች አንጻር ተመጣጣኝ ባይሆንም ፍትሃዊ የአየር ሰዓት ተመድቧል ማለት ይቻላል፡፡

እዚህ ላይ ግን ከበርካታ በዙሪያየ ካሉ ሰዎች የተለያዩ አስተያየቶችን አደምጣለሁ፡፡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ዋናው ጉዳያቸው ስፖርት ይመስል ወሪያቸው ሁሉ ስፖርት ሆነ የሚሉ አሉ፡፡

በእውነትም ፖለቲካዊ፣ማህበራዊ እና ምጣኔ-ሃብታዊ ጉዳዮችን እና ስፖርትን በአንድ ላይ ጨፍልቆ ለሚያቀርብ የሬድዮ ወይንም የቴሌቪዥን ጣቢያ ስፖርት ይህን ያህል የአየር ሰዓት ማግኘቱ የቀደመውን አስተያየት ሊያስነሳ ይችላል፡፡

ነገርግን ስፖርት በራሱ ካለው ዘርፈ ብዙ ጉዳይ አንፃር እንዲያውም ከላይ ከጠቀስኳቸው ሶስቱ ዋና ጉዳዮች ጋር መጨፍለቁ ተገቢዉን ትኩረት እንዳያገኝ አድርጎታል የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ፡፡

እንደሌሎች ሃገራት ስፖርታዊ ጉዳዮችን ብቻ የሚያቀርቡ የሬድዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አለመኖራቸው ተጎጂ እንዳደረገን አምናለሁ፡፡

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በሃገር ቤት እየተተገበረ ያለው የስፖርት ጋዜጠኝነት ምን ያህል ሙያዊ እና ስነምግባራዊ ነው ለሚለው እኔም በርካታ አሉታዊ አስተያየቶች አሉኝ፡፡

በአብዛኛው ለሃገርቤት መገናኛ ብዙሃን ስፖርት ማለት የእግር ኳስ ጨዋታ ሆኗል ያውም የአውሮፓ ክለቦች የእግር ኳስ ጨዋታ፡፡

የእግር ኳስ ጨዋታ ካለው አዝናኝነት፣ ከተመልካቹ ብዛት እና ከሚያንቀሳቅሰው ከፍተኛ ገንዘብ አንጻር በጋዜጣ ላይ የሰፋውን ቦታ እና በሬድዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ደግሞ የበዛውን የአየር ሰዓት ቢይዝ የጎላ ጥያቄ ላያስነሳ ይችላል፡፡

ሆኖም በእኔ ዳሰሳዊ ግምት በተለያየዩ የኤፍ ኤም እና የኤ ኤም ሬድዮ ጣቢያዎች ከሚቀርቡ የስፖርት ዝግጅቶች ብዙውን ግዜ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ እና አንድ አንድ ግዜ ከዘጠና በመቶ በላይ የእግር ኳስ ጉዳይ የሚተነተን ሲሆን ከዚህም የሚበዛው የአውሮፓ የእግር ኳስ ክለቦች ጨዋታ ጉዳይ ነው፡፡

ይህ የሆነበት ምክንያት በተለያዩ ጉዳዮች ተፅዕኖ ሊሆን ይችላል አንደኛ የእግር ኳስ በተለይም ደግሞ የአውሮፓ ክለቦች የእግር ኳስ ጨዋታ ከሌሎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የተሻለ አዝናኝ ነው ተብሎ ስለሚገመት፤ ሁለተኛ በሃገር ውስጥ አብዛኛው የስፖርት አድናቂ ማህበረሰብ የእግር ኳስን በተለይም ደግሞ የአውሮፓ ክለቦች የእግር ኳስ ጨዋታን የበለጠ ይወዳል ተብሎ ስለሚገመት፣ ሦስተኛ ደግሞ በተለይ ከአውሮፓ ሃገራት መገናኛ ብዙሃን የሚለቀቁ እጅግ ብዛት ያላቸው እና የየክለቦቻቸውን ሁኔታ የሚተነትኑ መረጃዎች በተትረፈረፈ ሁኔታ ማግኘት መቻሉ የጋዜጠኞችን ትኩረት በመሳቡ ሊሆን ይችላል፡፡

በእነዚህም ሆነ በሌሎች ምክንያት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን የአውሮፓ ክለቦችን የእግር ኳስ ጨዋታ ተንታኝ ሆኗል፡፡

የአውሮፓ ክለቦችን የእግር ኳስ ጨዋታ መተንተኑ ባይከፋም መገናኛ ብዙሃኑን በሚከታተለው ህብረተሰብ ዘንድ ሊፈጥር የሚችለው ተፅዕኖ ግን የተስተዋለ አሊያም በደንብ የተጠና አይመስለኝም፡፡

መረጃ ስለተገኘ ዝም ብሎ መተንተን ወይንም በመገናኛ ብዙሃን ማቅረብ ፋይዳው ምንድነው?

እከሌ የሚባለው ቡድን አሸነፈ ወይንም ተሸነፈ መባሉ መልካም ሆኖ ሳለ የእከሌው ቡድን ተጫዋች ወይንም አሰልጣኝ እንዲህ አለ ተብሎ መቅረቡ ለኢትዮጵያን የመገናኛ ብዙሃን ተከታታዮች ጥቅሙ ምንድን ነው?

እሱ እንዲህ ስላለ እና ምን ይሁን? ከዘገባው ጀርባ እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ የሚቻል ከሆነ የዘገባው ፋይዳ (impact) ተለይቷል ማለት ነው ሆኖም የአብዛኞቹ ዘገባዎች ፋይዳ ምን ስለመሆኑ አቅራቢዎቹም ተከታታዮቹም ስለማወቃቸው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡

በሚገርም ሁኔታ በአንድ አንድ የሃገር ውስጥ የስፖርት ጋዜጦች ደግሞ ሙሉ በሙሉ የአውሮፓ ክለቦች የእግር ኳስ ጨዋታ ጉዳዮች የሚቀርብባቸው ሲሆን የጋዜጣው ባለቤት አቋሙን በሚገልጽበት ኤድቶሪያል ላይ ግን ስለኢትዮጵያ ስፖርት አቋሙን ያቀርባል፡፡

በዘገቡት ጉዳይ ላይ አቋም መያዝ ሙያዊም ሞራላዊም ሲሆን ባልዘገቡት ጉዳይ ላይ አቋም መያዝ ግን አሁንም የዘገባ ፋይዳ የቱን ያህል እንደሆነ አለመረዳት ይመስለኛል፡፡

የሃገር ውስጥ ስፖርት የእግር ኳሱን ጨምሮ በአብዛኞቹ ስፖርታዊ ጉዳዮችን በሚያቀርቡ መገናኛ ብዙሃን ተገቢውን ትኩረት እያገኘ አይደለም፡፡

ይሄን ጉዳይ ቢያቀርቡ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ስለመቻላቸውም እርግጠኞች አይደሉም፡፡

በአንድ ወቅት የደከመ ወይንም የተሻለ ውጤት ሲያስመዘግብ ሚናቸውን ባልለየ መልኩ ከመጯጯህ እና አስተያየት ከመስጠት ባለፈ በአዘቦት ግዜያት የሃገር ውስጥ ስፖርት በሃገር ውስጥ የስፖርት መገናኛ ብዙሃን ችላ እንደተባለ ነው፡፡

ከዘህ በተረፈ ግን የሩጫ፣ የቴንስ፣ የቦሊቦል፣ የጎልፍ፣ የገና ጨዋታ፣ የፈረስ ጉግስ፣ የገበጣ ጨዋታ እና የሌሎችም ስፖርታዊ ጨዋታዎች አድናቂዎች እነዚህን ዘገባዎች ከሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ለማግኘት ቢያንስ በወር አንዴ መጠበቅ አሊያም ራሳቸው ጨዋታዎቹ የሚካሄዱባቸው ቦታዎች በመሄድ ከቦታው መረጃ ማግኘት ግድ ሳይላቸው አልቀረም፡፡

የስፖርት እና የጥበብ (ART) ጋዜጠኝነት ከሌላው የጋዜጠኝነት ሙያ በተለየ እና በተሻለ መልኩ ለጋዜጠኛው የሚሰጠው ነጻነት እና መብት አለ እሱም ሙያው ጋዜጠኞቹ በሚዘግቡት ጉዳይ ላይ የግል አስተያየታቸውን እንዲሁም ትችታቸውን በማካተት ማቅረብ እንዲችሉ መፍቀዱ ነው፡፡

ይህ ጋዜጠኞቹ ሊያቀርቡት የሚችሉት የግል አስተያየት እና ትችት በጉዳዮቹ መሰረታዊ ሃሳብ እና እውነታ ላይ ተነስተው የተደራጀ እና ከስሜት የፀዳ ሃሳብ ከመስጠት ስሜታዊ አስተያየት እስከመስጠት እንዲችሉ ይፈቅዳል፡፡

ለምሳሌ አንድ ስፖርት ጋዜጠኛ አንድን የእግር ኳስ ተጫዋች “ይህ ተጫዋች የእግር ኳስ ከሚጫወት ቢያርስ ይሻል ነበር” እስከሚል ስሜታዊ አስተያየት ቢሰጥ በህግም በሥም ማጥፋት ሊያስጠይቀው አይችልም፡፡

ሆኖም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ስፖርት የሚሉት እግር ኳስ ብቻ እንደሆነ እና እግር ኳሱም ያለው በአውሮፓ ክለቦች ዘንድ እንደሆነ እንቀበለው ብንልም እንኳ ይህንኑ የአውሮፓ ክለቦች እግር ኳስ የሚዘግቡበት መንገድም ግን የተሳሳተ ነው፡፡

የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል አንድ አንዶቹ የስፖርት ጋዜጠኞች “እኔ ብሆን ኖሮ ተጨዋቹ እንዲህ አደርግ ነበር፤ እኔ ብሆን ኖሮ አሰልጣኙ እንዲህ አይነቱን የጨዋታ አይነት እከተል ነበር” የመሳሰሉትን አስተያየት ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡ ይሄ የጋዜጠኝነት ሚናን አለመለየት ነው፡፡

አሱ ጨዋታው እንዴት እንደተካሄደ፣ ምን ጠንካራና ደካማ ጎኖች እንደነበሩት፣ ምን ክስተት ተፈጥሮ እንደነበር መረጃ አጠናቅሮ እና የራሱን አስተያየት አክሎ ሊነግረን ሲገባ እርሱ ቢሆን ኖሮ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ማውራቱ ማንነቱን ያለመለየቱ ችግር ይመስለኛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በስፖርት ዘገባዎች ላይ እውነታም አስተያየትም ያሆኑ ጉዳዮች ሲቀርቡ ይስተዋላሉ፡፡

ለምሳሌ ያህል “እከሌ የተባለው አሰልጣኝ እንደዚህ አስቦ ነበር፣ እከሌ የተባለው ተጫዋች ፍላጎት እንዲህ ነበር” የመሳሰሉ ነገሮች በስፖርት ጋዜጦች ተፅፈው ማንበብ እና በሬድዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሲነገሩ ማዳመጥ አዲስ አይደለም፡፡ በዚህ ግዜ እኔ የጋዜጠኞቹን ሰብዓዊ ፍጡርነት እጠራጠራለሁ፡፡

አንድ አሰልጣኝ የተናገረውን ለማወቅ ጋዜጠኛ መሆን በቂ ሲሆን ይህ አሰልጣኝ ያሰበውን ለማወቅ ግን አንድም አሰልጣኙ ይህን አስቢያለሁ ብሎ መናገር አለበት አንድም ጋዜጠኛው ሰው የሚያሰበውን የሚያውቅ የተለየ ፍጡር መሆን አለበት፡፡

እርግጠኛ ሆኜ ለመናገር ግን የአውሮፓ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች እንዲህ አይነት ዘገባ አያቀርቡም፡፡

ወገንተኛነት የሚስተዋልባቸው የጋዜጣ ሪፖርቶች፣ የሬድዮ የቀጥታ የስፖርት ስርጭቶች፣ እና የቴሌቪዥን ውይይቶችም የተለመዱ ሆነዋል፡፡

እነዚህን ዝግጅቶች የሚከታተሉ ሰዎች እከሌ የተባለው ጋዜጠኛ እከሌ ቡድን ደጋፊ ነው፣ እከሌ ደግሞ የእከሌን ቡድን ይጠላዋል ብለው በእርግጠኝነት መናገር እስኪችሉ ድረስ እነዚህ ወገንተኝነት የሚንጸባረቅባቸው ዘገባዎች አሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ዋናው ርዕሰ ጉዳይ ተረስቶ ከጨዋታው ጋር የማይያያዙ ጉዳዮች በበለጠ ትኩረት ሲዘገቡ ይስተዋላል፡፡

እከሌ የተባለው አንድ የአውሮፓ ክለብ ተጫዋች የሴት ጓደኛ ስትደሰት እና ስትበሳጭ ምን እንደምታደርግ ጠቀመውም አልጠቀመውም ለኢትዮጵያዊ ስፖርት ተከታታይ ይቀርብለታል፡፡

አሁንም ጠቀመውም አልጠቀመው ስለተጫዋቹ አባት፣ እናት እና ሌሎች ዘመዶች ማንነት እና ምንነት እንዲያነብ ወይንም እንዲያዳምጥ ይደረጋል፡፡

እጅግ የሚከፋው ግን እንዲህ ከላይ የጠቀስኳቸውን ስህተቶች በሙሉ ባካተተ መልኩ የሚተገበረው የስፖርት ጋዜጠኝነት ትክክለኛው ስፖርት ጋዜጠኝነት እንደሆነ እየተወሰደ መምጣቱ ነው፡፡

አንድ ጉዳይ በተሳሳት መልኩ በተደጋጋሚ ሲተገበር እና ለየት ባለ መልኩ በተስተካከለው መንገድ ጉዳዩን የሚያቀርበው ሲጠፋ ያ የተሳሳተ መንገድ በዘልማድ ተቀባይነት ያገኘ መንገድ ሆኖ ይቀጥላል፡፡

ስፖርት ጋዜጠኝነትም በዚህ መልኩ እየነጎደ ሲሆን ይኄ ሙያውንም ባለሙያውንም ቀስ በቀስ መጉዳቱ አይቀርም፡፡

እንደኛ ጥቂት የመገናኛ ብዙሃን ብቻ ባሉበት ሃገር ከሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች አንጻር እንደ ስፖርት እና ጥበብ በመሳሰሉ እና ከመንግስትም ሆነ ሌላ አካል ጋር ሊፈጥሩት የሚችሉት ግጭት አነስተኛ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ያሉ ዘገባዎች በዚህ መልኩ ሙያዊም ክህሎትም ሆነ ስነምግባራዊ ግዴታ የጎደላቸው ሆነው ሲገኙ የጋዜጠኞቹን እና መገናኛ ብዙሃኑን የብቃት ደረጃ ያጠያይቃል፡፡

Censorship: From institutionalized to internalized activity in Ethiopia.

Almost 20 years have passed since the revised Ethiopian constitution banned censorship in any means. However, new laws like, anti-terrorism and press law are forcing Ethiopian media to self- censorship.

It was an encouraging move for Ethiopian press after a long practice of socialist media philosophy when it is prohibited any form of censorship on article 29 by the new constitution of 1995 but, this move couldn’t go any further even after almost 20 years.

The biggest media in the country, Ethiopian Radio and Television Agency and the Press Agency are still under the control of the government. Most of the news, programs and articles by these media reflect the voice of the government in power.

Many of press freedom advocacy agencies criticize government is using the newly adapted laws like, anti-terrorism and press law for silencing the private press.

Journalists, bloggers and activities are arrested for “engaging” in the terrorism practice which is indicated in the controversial anti-terrorism law though; the government denies it has nothing to do with their professional activity in journalism.

These acts of the government are also intimidating the private press to freely criticize and comment on political and economic activities, according to unanimous sources.

Exiled journalists: The struggle to serve the public and tell the truth

The role of the journalist in exile is diverse and important. They have to help keep the Diaspora informed and also connect with the local population. However, a major obstacle is finding the resources to work efficiently.

Part of their role is to feed information from the country to those outside who require the information.  At the same time they process information from outside the country and relay that to the local community.

In this case, the audience is both the Diaspora and the local community who want to get connected and stay informed about what is going on people’s inside and outside the country.  

In many cases, Ethiopian exiled bloggers focus mainly on the Diasporas communities and the issues they face rather than on the country itself. Many of these bloggers are politically active.

Most of the issues that are covered by Ethiopian exiled bloggers are about politics, main opposition, and gossip. This could be because of the problem of accessing reliable and accurate information from domestic sources.

Free social media tools, however, offer the exiled journalist the chance to monitor material being posted from inside the country. They can use this to help with their new gathering, subject the usual fact checking requirements.

Ethics are important for the journalist in exile when reporting about domestic issue. They must not mislead or misinterpret events. However, most of the stories published by journalist in exile fail on this point and do not offer a fair opportunity for all sides to add their voice.  

የሃገር ቤት መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የጥሞና ግዜ ያስፈልጋቸው ይሆን?

ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት የአዲስ ነገር ጋዜጠኞች ከሃገር እንደተሰደዱ ሰሞን በፌስ ቡክ ገጻቸው ከፍተውት በነበረው የመወያያ ሰሌዳ ላይ አንድ መከራከሪያ ሃሳብ አቅርቤ ነበር፡፡

ሃሳቡን ጠቅለል አድርጌ ለማቅረብ ያህል ጥቃት እንደሚደርስብን ወይንም ልንታሰር እንደምንችል ጥቆማ ስለደረሰን ከዚህ ችግር ለመዳን መሰደድን መርጠናል ማለታቸው እርግጥ ትክክል ነው ወይ የሚል ሲሆን መሰደድ እስከመቼ መፍትሄ ሆኖ ሊቆይ እንደሚችልም ጠይቄያለሁ፡፡

ከሁለት ዓመት በሗላ ሰሞኑን ሁለቱ የጋዜጣው ባለደረቦች መስፍን ነጋሽ እና አብይ ተ/ማሪያም በሽብር ተጠርጥረው ክስ ሲቀርብባቸው ግን ቀደም ብየ የገለጽኩት ሃሳብ ግዜውን ያልጠበቀ እና ትንሽ ድፍረት የተቀላቀለበት ሙግት ስለነበር ይቅርታ መጠየቅ እወዳለሁ፡፡

በእርግጥ ከአዲስ ነገር ጋዜጠኞች በፊትም ሆነ እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ ከአዲስ ነገር ጋዜጠኞች በሗላ ስንት ጋዜጠኞች ተሰደዱ? ስንት ጋዜጦች ተዘጉ? የመገናኛ ብዙሃን ነጻነትስ የቱን ያህል አሽቆለቆለ?

በቅድመ 97 ምርጫ በዩኒቨርስቲ ትምህርት ላይ የነበርኩ ቢሆንም በወቅቱ የነበረውን ታላቅ መነሳሳት እና የመገናኛ ብዙሃን አስተዋፅኦ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለማጤን ሞክሬያለሁ፡፡

በቅድመ 97 ምርጫ ወቅት በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ታሪክ ጋዜጦች እና እንደ የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ እና የጀርመን ድምጽ ሬድዮ (ዶቼ ዋሌ) የመሳሰሉት ህዝብን በማነቃቃት ረገድ እጅግ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱበት ግዜ እንደነበር እሙን ነው፡፡

ከዚህም ባለፈ የህዝብ (የመንግስት) መገናኛ ብዙሃንም በተወሰ መልኩ ነጻነት እና ሙያዊ ስነምግባርን በተላበሰ አሰራር መረጃ ለማቀበል ይሞክሩ ነበር፡፡

ህዝቡም ጋዜጦችን ለማንበብ፤ ሬድዮችን ለማዳመጥ እንዲሁም በእነዚህ መገናኛ ብዙሃን የቀረቡ መረጃዎች ላይ ለመወያየት የነበረው ትጋት እና ተነሳሽነት እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡

ብዙዎቻችን እንደምናውቀው በድህረ 97 ምርጫ የነበረው ሁሉ እንዳልነበረ ሆኖ የነበሩት በርካታ ጋዜጦች ለመዘጋት፤ ሬድዮኖች ለመታፈን እና ጋዜጠኞች ለመሰደድ ተዳረጉ፡፡

ነገር ግን የቅድመ እና ድህረ 97 ምርጫ ልምድ ትቶልን ያለፈው ትልቅ ትምህርት ያለ ይመስለኛል፡፡ ህዝብ በመገናኛ ብዙሃን ላይ እምነት ሲያሳድር መገናኛ ብዙሃኑ ላይ ከባድ ሃላፊነት እየጣለባቸው ነው፡፡

መገናኛ ብዙሃን ያላቸው ትልቁ ጉልበት አጀንዳ የመቅረፅ ሲሆን ይህንን የቀረጹትን አጀንዳ ከብዙ አቅጣጫ መዝኖ፣ ተንትኖ እና በርካታ መረጃ አካቶ ማቅረብ ደግሞ ሃላፊነታቸው ነው፡፡

መገናኛ ብዙሃን ያቀረቡትን መረጃ ተንተርሶ ደግሞ ህዝቡ ይወያያል፤ አቋም ይይዛል፤ ሃሳቡን ይቀይራል ወዘተ… ይህ ማለት መገናኛ ብዙሃን የመሪነት ሚና አላቸው ማለት ነው፡፡

አሁን ጥያቄው በቅድመ 97 ምርጫ መገናኛ ብዙሃን ምን ያህል የመሪነት ሚናቸውን ተወተዋል የሚል ነው?

በእኔ እምነት ለመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ማሽቆልቆል፣ ለበርካታ ጋዜጦች መዘጋት፣ ለጋዜጠኞች መሰደድ እና መታሰር በህግም በሞራልም ትልቁ ተጠያቂ እና ባለድርሻ መንግስት ሆኖ ሳለ የመገናኛ ብዙሃኑም በሞራል ተጠያቂ ናቸው፡፡

መንግስት የመገናኛ ብዙሃን ነጻነትን ማፈኑ እርግጥ ቢሆንም መገናኛ ብዙሃኑ ነጻነታቸውን ለማጣት የቱንም ያህል ቢሆን የራሳቸው አተዋፅኦ አለበት፡፡ ይህን ስል የመንግስትን ጫና እያቃለልኩ ወይንም መገናኛ ብዙሃኑን እየወነጀልኩ አይደለም፡፡

በመንግስት በኩል ያለውን ጫና ፀሃይ የሞቀው አገር ያወቀው ነውና እሱን ወደ መተንተን አልሄድም ነገር ግን የመንግስትን ጫና ለማስወገድ ከመታገል ጎን ለጎን ሰከን ባለ መንፈስ መገናኛ ብዙሃን የራሳቸውን ችግር ለመፍታት እና ስልታዊ አካሄድ ለመንደፍ በግፅል መነጋገር ያስፈልገል ብየ አምናልሁ፡፡

ከላይ እንዳሰፈርኩት መገናኛ ብዙሃን የመሪነት ሚና አላቸው ነገር ግን ምን ያህል ሃላፊነት እና ስልታዊ አካሄድ ባለው መልኩ ሚናቸውን ተወተዋል የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡

መገናኛ ብዙሃን አጀንዳ የመቅረፅ ትልቅ ሃይል ቢኖራቸውም ከዚህ ሃይል ባልተናነሰ መልኩ ደግሞ ሃላፊነት የሚባል ትልቅ እዳ አለባቸው፡፡ እንዲያውም መገናኛ ብዙሃን ሃላፊነት የማይሰማቸው ከሆነ ነጻነት ባይኖር ይሻላል በሚል አንድ አንዶች ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ሃሳብ እኔም እስማማለሁ፡፡

መንግስትም መገናኛ ብዙሃን በሃላፊነት መስራት እንደሚገባቸው በበዙ ሲሰብክ ይሰማል፡፡ ነገር ግን መንግስት ይህን ሃሳብ ለራሱ ጥቅም በሚያደላ መልኩ ለመተርጎም ይመቸዋል፡፡

መገናኛ ብዙሃን አጀንዳ መቅረጽ ሲገባቸው የህዝቡን አጀንዳ የሚከተሉ ከሆነ ህዝብ እየመራ እና መገናኛ ብዙሃን እየተመሩ ነበር ማለት ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚ ለሚደርስ ስህተት ደግሞ ሃላፊነቱን ሊውስድ የሚችለው አካል ራሱ መገናኛ ብዙሃኑ ሲሆን ይሄኔ ራሳቸውን ለጥቃት አመቻቹ ማለት ነው፡፡

በእርግጥ ህዝብን መምራት ማለት በራሱ ከባድ ሃላፊነት ነው አንድም ህዝብን ለመምራት ከህዝብ ቀድሞ መገኘት ይጠበቃል፣ አንድም የሚመራበትን መንገድ ማወቅ ያስፈልጋል፣ አንድም ህዝቡን መርቶ የት እንደሚያደርስው መሪው ማወቅ አሊያም በትክክል መገመት ይጠበቅበታል፡፡

ነገርግን በቅድመ 97 ምርጫ የነበሩት መገናኛ ብዙሃን ህዝብን ለመምራት እነዚህን ሶስት ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ ስለማሟላታቸው እጠራጠራለሁ፡፡

መገናኛ ብዙሃን ነበሩ አጀንዳ የሚቀርጹት ብንል እንኳ የሚቀርቡ መረጃዎች እና ትንታኔዎች ከስሜታዊነት እና ወገንተኝነት ነጻ ካልሆኑ ወይንም በደንብ ካልተጤኑ ህዝቡን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እየመሩት እራሳቸውንም ለአደጋ እያመቻቹ ነበር፡፡

ሌላው መገናኛ ብዙሃኑ እርስ በእርስ የነበራቸው ትብብር እና መናበብ እጅግም ትኩረት የተሰጠበት ጉዳይ አልነበረም፡፡

ለዚህ ማስረጃ የሚሆንው ደግሞ በድህረ 97 ምርጫ ጋዜጦች ሲዘጉ እና ጋዜጠኞች ሲታሰሩ ሌሎች መገናኛ ብዙሃን በተናጥል እከሌ ጋዜጣ ተዘጋ እከሌ የተባለው ጋዜጠኛ ደግሞ ታሰረ ብሎ ከመዘገብ ባሻገር በጋራ አቋም ያወጡበት፣ ያወገዙበት እና ፍትሃዊ ዳኝነት እንዲያገኙ የዘመቱበት ሁኔታ ጎልቶ አልታየም፡፡

ለዚህ አንዱ እና ዋነኛው ምክንያት ደግሞ በግለሰቦች ማንነት እና አቋም ላይ የተመሰረቱ የጋዜጠኛ ማህበራት መብዛት እና ማህበራቱ ለቆሙለት አላማ ከመታገል ይልቅ አብዛኛውን ጊዜያቸውን እርስ በእርስ ለመፎካከር እና ለመወነጃጀል ስለሚያውሉት አቅማቸውን ሊጠቀሙበት አለመቻላቸው ነው፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባለ ታዳጊ ሃገር መንግስት እጅግ ገዝፎ ይታያል፡፡

ይህን ግዙፍ አካል እጅግም ቢተጋ አንድ ጠንካራ ጋዜጠኛ ወይንም አንድ ጠንካራ ጋዜጣ ብቻውን ሊጋፈጠው አይችልም፡፡

በቅድመ 97 ምርጫ ብዙ ጋዜጣ ሆነው በድህረ 97 ምርጫ ደግሞ እንደ አዲስ ነገር እና አውራምባ ታይምስ የመሳሰሉ ጥቂት ጋዜጦች ይህንን ሞክረውት አልቻሉም፡፡

የመገናኛ ብዙሃንን ነጻነትን ለማስከበር የጋዜጦች መብዛት እና የጋዜጠኞች መጠንከር አስፈላጊ ጉዳይ ቢሆንም እርስ በእርስ መተባበር ፣ መቀናጀት እና አንዱ ለሌላው መብት በጋራ መሟገትም ግድ ይላል፡፡

ካልሆነ ግን አንዱ የቻለውን ሞክሮ ሲደክም ሲወጣ እና ሌላው ለመግባት ሳይደፍር በተለይ የግሉ መገናኛ ብዙሃን ተገዶም ሆነ ወዶ ሙሉ ለሙሉ እጅ ሊሰጥ ነው ማለት ነው፡፡

እንደ እኔ እምነት እጅግ በጣም ቢዘገይም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እና የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ቡድኖች ያለፉትን ግዜያት በሰከነ መንፈስ የሚገመግሙበት እና አዲስ ስልታዊ አካሄድ (strategy) የሚነድፉበት ወቅት ነው፡፡

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እና የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቾች ስልታዊ አካሄድ መንደፍ የነበረባቸው ግዜ በመዘግየቱ አሁንም ጋዜጦች እየተዘጉ ነው አሁንም ጋዜጠኞች እየተሰደዱ እና እየታሰሩ ነው፡፡

ሁሉም ተዘግተው፣ ተሰደው እና ታስረው ከማለቃቸው በፊት ግን አሁንም ቢሆን ስልታዊ አካሄድ መንደፍ ያስፈልጋል፡፡

ስልታዊ አካሄድ ሲነደፍ መገናኛ ብዙሃን ያላቸውን ጠንካራ እና ደካማ ጎን መለየት ያስችላቸዋል ከዚህም በተጨማሪ ያሉትን ስጋቶች እና እድሎች መለየት ይቻላል፡፡ ከዚህ በመነሳት ደግሞ ወደፊት በምን በልኩ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አቅጣጫ መጠቆም ይቻላል፡፡

ስልታዊ አካሄድ የተናጥል እሩጫን በማስቀረት የነሰናሰለ (harmonious) ህብረት ያለው እንቅስቃሴ እንዲኖር ያስችላል፡፡

ይህ በመጀመሪያ ደረጃ ሙያውን (ጋዜጠኝነትን) ለማስከበር ይጠቅማል ከዚህ በመቀጠል ግን ለባለሙያው ከለላ ለመስጠት እንዲሁም መገናኛብዙሃኑን ከውድቀት ለመከላከል ይረዳል፡፡

እዚህ ላይ ግን መንግስት የሰራውን ስህተት ላለመድገም እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያሻል፡፡ ለምሳሌ መንግስት የራሱን (የህዝብን) መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን አቅርቦ የግሉ መገናኛ ብዙሃንን አግልሏል፡፡

እርግጥ ነው በመንግስት መገናኛ ብዙሃን የተሰገሰጉ “ልማታዊ ጋዜጠኛ” የሚል አዲስ ስም የተሰጣቸው እና ለመንግስት ወይንም ገዢው ፓርቲ የቆሙ በረኞች (Gatekeepers) አሉ፡፡

እነዚህ በረኞች እርግጥ ጋዜጠኛ ናቸው ወይ ብለን ብንጠይቅ አይደሉም ነገርግን ማንኛውም አምባገነን መንገስት “ልማታዊ ጋዜጠኛ” የሚልም ሆነ ሌላ ተቀጥላ ስም እየሰጠ በረኞችን መጠቀሙ የነበረ ልምድ ነው፡፡

ይህ ማለት ግን በመንገስት (የህዝብ) መገናኛ ብዙሃንም እውነተኛ ጋዜጠኞች እና ባለሙያዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ትልቁ የሞራል ልዕልና እነዚህን ጋዜጠኞችም ማሳተፍ መቻል ነው፡፡

ወቅታዊውን የመገናኛ ብዙሃን ፍልስፍና እና የእድገት ደረጃ ከሃገር ቤት እውነታ እና ግንዛቤ አንጻር መቃኘትም ወሳኝ ይመስለኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት የመገናኛ ብዙሃን ፍልስፍና እየተለወጠ መጥቷል፤ የመገናኛ ብዙሃን እድገት በተለይ በቴክኖሎጂ ረገድ እጅግ መጥቋል ነገር ግን በእኛ ሃገር አሁንም ለየት ያለ ነገር ሲጻፍ ገና “ይሄ ሰው ምነው ተዳፈረ?” የሚባልበት ደረጃ ላይ ነን፡፡

በአደጉት ሃገራት መገናኛ ብዙሃን የማስተማር ሚናቸው እጅግ እደበዘዘ የመጣ ቢሆንም የእኛን በመሳሰሉ ታዳጊ ሃገራት ግን አሁንም መገናኛ ብዙሃን ዋና ማስተማሪያ መሳሪዎች ናቸው፡፡

እነዚህን ጉዳዮችም ስልት ሲነደፍ ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል፡፡

አሁንም አጽዕኖት ልሰጥበት የምፈልገው ጉዳይ ግን ስልት መንደፊያው ጊዜ ዘግይቷል፤ ከአሁን በሗላም እንዴት ተሰባስቦ ስልት መንደፍ እንደሚቻል እርግጠኛ አይደለሁም፡፡

ነገር ግን እድሜ ለዘመኑ ቴክኖሎጂ እንደዚህ በመሳሰሉ ብሎጎች እና የማህበረሰብ ድረ-ገጾች በመሟገትም ቢሆን ትንሽ እርቀት መጓዝ ይቻላል፡፡

Et_papers_123
Et_papers_123